Skip links

ስራዎቻችን

ቁልፍ ስትራቴጂ

ተደራሽነት

የስርጭት ሰንሰለቱን በማጠናከር እና አማራጮችን በማስፋት ጥራታቸውን የጠበቁ ኮንዶሞች፣ የእርግዝና መከላከያ ዘዴዎች እንዲሁም የእናቶችና ህፃናት ጤና ምርቶች አቅርቦትን ማሳደግ፡፡

ፍላጎት

የመገናኛ ብዙሃን እና ትምህርታዊ ዘመቻዎችን በመጠቀም ለስነተዋልዶ ጤና ምርቶች ያለውን ፍላጎት ማሳደግ፡፡

አቅም

ስልጠናና ድጋፍ በማድረግ የጤና አገልግሎት ሰጪዎችን ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት የማቅረብ አቅም ማሳደግ፡፡

ዘላቂነት

ስራ ፈጣሪ፣ ችግሮችን የሚጋፈጥ እና ውጤት ተኮር የንግድ ግብይት ስልቶችን መተግበር፣
የግሉን ዘርፍ የቤተሰብ እቅድና የስነተዋልዶ ጤና ምርቶችና አገልግሎቶች አቅርቦት ማሳደግ፡፡

የፕሮግራም ትኩረቶች

የዲኬቲ ማህበራዊ ግብይ ፕሮግራም በአራት አበይት ጉዳዮች ላይ ያተኩራል

የዘመናዊ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ዘዴዎችን ተጠቃሚነት መጨመር

ዲኬቲ በማህበራዊ ግብይት ትስስሮች አማካኝነት በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ጥንዶችና ግለሰቦች የተሟሉ የአጭር እና የረጅም ጊዜ የእርግዝና መከላከያ ዘዴዎችን ተደራሽነት፣ ፍላጎትና ተጠቃሚነት ለመጨመር እየሰራ ነው፡፡ ለዚህም በእርግዝና መከላከያ ምርቶች ስርጭቱ በሺዎች የሚቆጠሩ የጤና ተቋማትን በመደበኛነት ይደርሳል፡፡ የእርግዝና መከላከያ ምርቶች ፍላጎትን ለመጨመር እና ለአገልግሎት ሰጪዎች ስልጠናዎችን ለማዳረስ 360 ዲግሪ ማርኬቲንግ ስራዎችን ይሰራል፡፡ ከ100 በላይ የሚሆኑት የዲኬቲ አጋር ክሊኒኮች ኔትወርክ በግል ክሊኒኮች የረጂም ጊዜ የእርግዝና መከላከያ ዘዴዎችን እንዲሁም የእናቶችና ህፃናት ጤናን ለማሳደግ ከሚከተላቸው ቁልፍ ስትራቴጂዎች አንዱ ነው፡፡

የኤችአይቪ ኤድስ እና የአባላዘር በሽታዎችን ስርጭት እንዲሁም ያልታቀደ እርግዝናን መቀነስ

የኢትዮጵያ መንግሥት የኤች.አይ.ቪ / ኤድስ ብሔራዊ ስትራቴጂክ ዕቅድ አፈፃፀምን ለማሳደግ ዲኬቲ ጥራት ያላቸውን ኮንዶሞች እና የማለስለሻ ቅባቶችን ተደራሽነትና አጠቃቀምን ማሻሻሉን ቀጥሏል፡፡ ዲኬቲ በአስር ሺዎች ለሚቆጠሩ የግል ህክምና እና የንግድ ማሰራጫዎች ኮንዶሞችን የሚያቀርብ ሲሆን ያንግ ማርኬተርስ (ዋይ ኤም) ክበቦችን ደግሞ በሆቴሎች፣ ባሮች፣ ፔንሲዮኖች (እንግዳ ማረፊያዎች) እና ኪዮስኮች ወጪ ቆጣቢ በሆነ መልኩ ኮንዶሞችን ለማቅረብ ይጠቀማል፡፡ ይህ የኮንዶሞችና ቅባቶች ስርጭት በሰፊ የቴሌቪዥንና ራዲዮ ማስታወቂያዎች፣ በቢልቦርዶች፣ ብርሃናማ የማስታወቂያ ሳጥኖች እና የተጠኑ የባህሪ ለውጥ የተግባቦት ስራዎች የተደገፈ ነው፡፡

ብሔራዊ ስትራተጂክ ዕቅዱ ቁልፍና ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገባ ብሎ በለያቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ላይም ዲኬቲ በተጠና መልኩ ይሰራል፡፡ እነዚህም የሚከተሉትን ያካትታሉ፡፡

  • ሴተኛ አዳሪዎች እና ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው የሚሰሩ ሰዎች
  •  በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ያሉ ተማሪዎችን ጨምሮ ወጣቶችና በአፍላ እድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች
  •  የግንባታ እና ኢንዱስትሪ ፓርክ ሰራተኞች
  •  ወታደሮችና ፖሊሶች
የእናቶች ጤና ምርቶች አጠቃቀምን ማሻሻል

ኢትዮጵያ ውስጥ የደም መፍሰስ፣ በእርግዝና ወቅት የሚከሰት የደም ግፊት፣ ውርጃ እና ከባድ ኢንፌክሽን (sepsis) ዋነኞቹ የእናቶች ሞት ምክንያት መሆናቸውን ቀጥለዋል፡፡ እነዚህ ችግሮች ሊቀረፉ የሚችሉት በህክምና እርዳታ ብሎም አስተማማኝ የውርጃ እና የድህረ ወሊድ የደም መፍሰስ መከላከል አገልግሎቶችን ተደራሽነት በማስፋት ነው፡፡ በአፍላ እድሜ ላይ የሚገኙ ወጣት ሴቶች በ1997 ዓ.ም ከተደረገው የኢትዮጵያ የውርጃ ህግ መሻሻል በከፍተኛ ሁኔታ እንደተጠቀሙና ባለፉት ሶስት አስርት አመታት የእናቶች ሞት እየቀነሰ መሆኑን የተለያዩ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

የኢፌዲሪ ወንጀለኛ መቅጫ ህግ አንቀፅ 551 ከዚህ በታች በተጠቀሱት ሁኔታዎች የፅንስ መቋረጥን ይፈቅዳል፡፡

  • በአስገድዶ መደፈር ወይም በዘመድ መካከል በተደረገ የግብረስጋ ግንኙነት ምክንያት ፅንሱ የተገኘ ሲሆን
  •  የእርግዝናው መቀጠል በእናቲቱም ሆነ በፅንሱ ህይወት ወይም በእናቲቱ ጤንነት ላይ አደጋ የሚያስከትል ሲሆን ወይም የልጁ መወለድ የእናቲቱ ጤንነት ወይም ህይወት ላይ አደጋ የሚያመጣ ሲሆን
  •  ፅንሱ ሊድን የማይችል ከባድ የአካል ጉድለት ያለው ሲሆን ወይም
  •  አንዲት እርጉዝ ሴት የአካል ወይም የአእምሮ ጉድለት ያለባት በመሆኗ ወይም ለአካለ መጠን ያልደረሰች በመሆኗ የሚወለደውን ህፃን ለማሳደግ የህሊናም ሆነ የአካል ዝግጁነት የሌላት ሲሆን ናቸው፡፡

በመድሃኒት የሚከወን የፅንስ ማቋረጥ ኪቶችን፣ በመሳሪያ የታገዘ የፅንስ ማቋረጥ ኪቶችን እና ከወሊድ በኋላ የሚከሰት የደም መፍሰስን ለመከላከል የሚያገለግሉ ሚሶፕሮስቶል እንክብሎችን ጨምሮ አስተማማኝ የፅንስ ማቋረጫ ምርቶችን ተደራሽነት ለመጨመር ይሰራል፡፡በመድሃኒት የሚከወን የፅንስ ማቋረጥ እና የተሟላ የፅንስ ማቋረጥ እንክብካቤ ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ አገልግሎት ሰጪዎችን ከማሰልጠኑም በላይ ደህንነቱ ስለተጠበቀ የፅንስ ማቋረጥ ሂደት መረጃ የሚሰጡ የተለያዩ ሰነዶችን ያዘጋጃል፡፡

የህፃናትን ሞትና ህመም መቀነስ

የህፃናትን ህመምና ሞት በመቀነስ ረገድ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ውጤት አስመዝግባለች፡፡ ይህም ወባን መከላከልና መቆጣጠር፣ ማህበረሰብን መሰረት ያደረገ የተመጣጠነ ምግብ፣ የአራስ ህፃናት ክብካቤ ክፍሎች መቋቋም እና አጣዳፊ የመተንፈሻ አካላት በሽታ እና ተቅማጥ ችግሮች ተገቢ አያያዝን ጨምሮ መከላከል ላይ ያተኮረ እና ፈዋሽ የመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ ተግባራዊነት ውጤት ነው፡፡ የኢኮኖሚ እድገቱም የራሱን አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡

በኢትዮጵያ ለህፃናት ሞት ዋነኛ ምክንያት ከሆኑት መካከል አንዱ የሆነውን የተቅማጥ በሽታ ለማከም በማህበራዊ ግብይት የሚቀርብ ህይወት አድን ንጥረነገር (ኦአርኤስ) ተደራሽነትን ለማስፋትም እየሰራ ይገኛል፡፡ ህይወት አድን ንጥረነገር (ኦአርኤስ) በተቅማጥ በሽታ ሊከሰት የሚችለውን የሠውነት ፈሳሽ እጥረት ይተካል፡፡ በሀገሪቱ ከአስር ህፃናት ሶስቱ ኦአርኤስን ለተቅማጥ በሽታ ይወስዳሉ፡፡ ዲኬቲ በወላጆች ዘንድ ግንዛቤ ለመፍጠር የተለያዩ ኦአርኤስን የማስተዋወቅ ስራዎችን ከመስራቱም ባሻገር ለጤና አገልግሎት ሰጪዎችም ስልጠናዎች ይሰጣል፡፡