ሌቮፕላንት አስተማማኝ እና ከፍተኛ ውጤታማነት ያለው በሴቷ የክንድ ቆዳ ስር የሚቀመጥ ባለነጠላ አካላዊ ቅመም የእርግዝና መከላከያ ነው ሲሆን በተፈለገ ጊዜ አስወጥቶ ማርገዝ ይቻላል፡፡ ሌቮፕላንት የተሰራው በተፈጥሮ በሴቶች አካል ውስጥ የሚመረተውን ፕሮጀስትሮን ሆርሞን (አካላዊ ቅመም) ከሚመስል ፕሮጀስቲን የተባለ በሳይንሳዊ መንገድ የተፈበረከ ንጥረነገር ነው የያዙ ሁለት ቀጫጭን የክብሪት እንጨት የሚያክል መጠን ያላቸው የታሸጉ፣ ከማናቸውም ባክቴሪያና ረቂቅ ተህዋሲያን የፀዱ ፣ ተጣጣፊ፣ ነጫጭ ክብ ዘንጎች ነው፡፡ እያንዳንዱ ዘንግ 75ሚ.ግ ሌቮኖርጀስትሪል አካላዊ ቅመም ያያዘ ነው፡፡ ሆርሞኑ በዝግታ እና ቀጣይነት ባለው መልኩ ለሶስት አመታት ያህል እየተለቀቀ እርግዝናን ይከላከላል፡፡ ሶስት አመት ከሞላው በኋላ ከሴቷ ክንድ ውስት መውጣት ያለበት ሲሆን ሴቷ በቀጣይነት መጠቀም ከፈለገች በአዲስ መተካት ይኖርበታል፡፡
በክንድ ቆዳ ስር ውስጥ የሚቀመጥ
ሌቮፕላንት
አስተማማኝነቱ ምን ያህል ነው?
ሌቮፕላንት እጅግ ውጤታማ ከሚባሉ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ዘዴዎች አንዱ ነው፡፡ በአንድ አመት ውስጥ ሌቮፕላነትን ከሚጠቀሙ ሴቶች ውስጥ እርግዝና የመከሰት እድሉ ከ1 ከመቶ በታች ሲሆን አብዛኛው የሚከሰተውም ትክክል ባልሆነ አገባብ እና ሴቷ እርጉዝ መሆን አለመሆኗ ሳይረጋገጥ በክንዷ ውስጥ ከተቀመጠ ነው፡፡
ሴቷ ማርገዝ በፈለገችበት ጊዜ ሌቮፕላንትን ከክንዷ ውስጥ በማስወጣት ማርገዝ ትችላለች፡፡
ሌቮ ፕላንት ከኤችአይቪ/ኤድስና ከአባላዘር በሽታወች አይከላከልም፡፡
ጤና ነክ ጥቅሞች
እርግዝናን ከመከላከል ባሻገር ሌቮፕላንት በአይረን እጥረት ምክንያት የሚከሰት የደም ማነስን ሊከላከል ይችላል፡፡
ከሌሎች መድሃኒቶች ጋር ያለ ተቃርኖ
አንዳንድ መድሃኒቶች በክንድ ቆዳ ስር የሚቀመጡ የእርግዝና መከላከያ ዘዴዎችን ውጤታማነት ይቀንሳሉ፡
- Anti-epilepsy drugs የሚጥል በሽታ መድሃኒቶች
- Carbamazepine
- valproic acid
- Barbiturates (phenobarbital) የእንቅልፍ መድሃኒቶች
- Phenytoin
- Antibiotics: ፀረ ባክቴሪያዎች
- Rifampicin
- Griseofulvin (ፀረ ፈንገስ)
ሌቮፕላንትን መጠቀም የሚችሉት እነማን ናቸው
ሌቮፕላንት በመውለድ እድሜ ክልል ውስጥ ላሉ ሴቶች ሁሉ ለማለት በሚያስችል ደረጃ ተስማሚና ምቹ የእርግዝና መከላከያ ነው፡፡
- በማንኛውም የእድሜ ደረጃ ላይ የሚገኙ
- ልጅ ያላቸው ወይም የሌላቸው
- ያገቡ ወይም ያላገቡ
- ፅንስ ያቋረጠች ወይም ያስወረዳት ሴት
- ጡት የሚያጠቡ እናቶች (ልጅ ከወለዱ ከስድስተኛው ሳምንት ጀምሮ)
- ሲጋራ የሚያጨሱ ሴቶች
- የፀረ -ኤች አይ ቪ መድሀኒት ቢወስዱም ባይወስዱም የኤች.አይ.ቪ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ ያለባቸው ሴቶች ሌቮፕላንትን መጠቀም ይችላሉ፡፡
ሌቮፕላንትን መጠቀም የማይችሉት እነማን ናቸው
ከዚህ በታች ከተዘረዘሩት ውስጥ አንዱን የምታሟላ ሴት ማንኛውንም በክንድ ቆዳ ስር የሚቀመጥ የእርግዝና መከላከያ መጠቀም የለባትም፡፡
- የምታጠባና ከወለደች ከ6 ሳምንት በታች የሆናት ሴት
- የደም መርጋት ችግር ያለባት ሴት
- መንስዔው ያልታወቀ የማህፀን መድማት ችግር
- ባለፉት አምስት አመታት ውስጥ የጡት ካንሰር ህመም የነበረባት ሴት
- ከባድ የጉበት ህመም፣ ኢንፌክሽን ወይም ዕጢ ያለባት ሴት
- barbiturates, carbamazepine, oxcarbazepine, phenytoin, primidone, topiramate, or rifampicin መድሃኒቶች የምትወስድ ሴት
የጎንዮሽ ችግሮች
- ራስ ምታት
- በወር አበባ ላይ የሚታዩ ለውጦች (ለረጅም ቀናት የወርአበባ መፍሰስ፣ የወር አበባ አለመምጣት፣ መደበኛ ያልሆነ የወር አበባ ፍሰት)
- የስሜት መለዋወጥ
- ማቅለሽለሽ
- ድብርት
- ብጉር
- የክብደት መጨመር
- የጡት መደደር