Skip links
በአፍ የሚወሰዱ እንክብሎች 

አይፕላን

አይፕላን በአፍ የሚወሰድ ባለነጠላ አካላዊ ቅመም የእርግዝና መከላከያ እንክብል ሲሆን፤ የተሰራውም በተፈጥሮ በሴቶች አካል ውስጥ የሚመረተውን ፕሮጀስትሮን አካላዊ ቅመም (ሆርሞን) ከሚመሳሰል በጣም ዝቅተኛ መጠን ካለው ፕሮጀስቲን የተባለ በሳይንሳዊ መንገድ የተፈበረከ ንጥረ ነገር ነው፡፡

እያንዳንዱ የአይፕላን እሽግ ባለ 28 ፍሬ ሲሆን፤ ይዘታቸው ሌቮኖርጀስትሪል 0.03 ሚ.ግ የሆነ የእርግዝና መከላከያ እንክብሎችን ይይዛል፡፡

አይፕላን ለሚያጠቡ እናቶች እርግዝናን ለመከላከል ይጠቅማል፡፡ ሴቷ በወለደች ከስድስተኛው ሳምንት ጀምሮ አይፕላንን መጠቀም ትችላለች፡፡

አስተማማኝነቱ ምን ያህል ነው?

አስተማማኝነቱ እንደ ተጠቃሚዎቹ የአጠቃቀም ሁኔታ ይወሰናል: የወር አበባቸው በየወሩ ለሚመጣ እና አይፕላንን ለእርግዝና መከላከያ ለሚጠቀሙ ሴቶች አይፕላን ሙሉ በሙሉ ካልተወሰደ ወይም መወሰድ ካለበት ጊዜ ዘግይቶ ከተወሰደ እርግዝና የመከሰት ዕድሉ ከፍተኛ ነው፡፡ አይፕላንን ከሚጠቀሙ የሚያጠቡ እናቶች መካከል በመጀመሪያው ዓመት እርግዝና የመከሰት እድሉ 0.5% ነው፡፡ የአይፕላን እንክብል ስትጠቀም የነበረች ሴት እንክብሉን መውሰዷን በመተው ለማርገዝ ብትፈልግ ወዲያውኑ ማርገዝ ትችላለች፡፡ አይፕላን ኤች.አይ.ቪን ጨምሮ ከማንኛውም ተላላፊ የአባላዘር በሽታዎች አይከላከልም፡፡

ጤና ነክ ጥቅሞች

አይፕላን እርግዝናን ከመከላከል በተጨማሪ የሚከተሉትን የጤና ችግሮች ለመከላከል ይረዳል፡-

  • ከኢስትሮጅን ጋር ተያያዥ የሆኑ የጎንዮሽ ችግሮችን
  • ካንሰር ያልሆኑ የጡት ህመሞችን (Benign breast disease)
  • የማህፀን ግድግዳ ካንሰር
  • የእንቁልጢ ካንሰር

አይፕላንን መጠቀም የሚችሉት እነማን ናቸው

  • ጡት የሚያጠቡ ሴቶች (ልጅ ከወለዱ ከስድስተኛ ሳምንት ጀምሮ)
  • ልጅ ያላቸው ወይም የሌላቸው
  • ያገቡ ወይም ያላገቡ
  • አፍላ ወጣቶች እና ከ40 አመት በላይ የሆናቸው ሴቶችን ጨምሮ በማንኛውም የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሴቶች
  • በማንኛውም የዕድሜ ክልል ያሉ ሲጋራ የሚያጨሱ ሴቶች
  • ፅንስ ያቋረጠች ወይም ያስወረዳት ሴት
  • የደም ማነስ ያለባቸው ወይም በፊት የነበረባቸው ሴቶች

አይፕላንን መጠቀም የማይችሉት እነማን ናቸው

  • ያረገዘች ወይም እንዳረገዘች የምትጠረጠር ሴት
  • የጉበት ህመም ያለባቸው ሴቶች
  • ጉበት መደበኛ ስራውን በትክክል ማከናወን የማይችልበት ሁኔታ ላይ ካለ
  • መንስኤው ያልታወቀ የማህፀን መድማት ችግር ካለ
  • የደም መርጋትና ከደም መርጋት ጋር የተቆራኘ የውስጥ ደዌ ችግር ካለ
  • ከፍተኛ የደም ግፊት ካለ
  • ከፍተኛ የራስ ህመም ወይም ጭንቅላትን ከፍሎ የሚያም የራስ ምታት ካለ ወይም ከነበረ
  • እንክብሉ የተሰራበት ንጥረነገሮች እንደማይስማማት የተረጋገጠ ሴት

የጎንዮሽ ችግሮች

በወር አበባ ላይ የሚከሰቱ ለውጦች

ለምሳሌ፡-

  • ለተወሰነ ጊዜ የወር አበባ መቅረት
  • ለሚያጠቡ እናቶች የወር   አበባ ዘግይቶ መምጣት
  • ህመም ያለው የወር አበባ
  • መጠነኛ የራስ ምታት
  • ድብርት
  • ማቅለሽለሽ (በአብዛኛው ከ2-3 ወራት ጊዜ ውስጥ ይህ ስሜት ይጠፋል)
  • ማስመለስ
  • የሆድ ቁርጠትና የሆድ መነፋት
  • የጡት መደደር
  • መጠነኛ የክብደት መጨመር ወይም መቀነስ

ስለ አይፕላን ተደጋግመው የሚጠየቁ ጥያቄዎች

አይፕላን በጡት ወተት ብዛትም ሆነ ጥራት ላይ የሚያስከትለው ምንም ዓይነት ለውጥ የለም፡፡

ሴቷ በዚያ ቀን የግብረ ስጋ ግንኙነት ብታደርግም ባታደርግም አይፕላንን በየቀኑ መውሰድ አለባት፡፡

አንድ ሴት አይፕላንን መጠቀም ካቆመች በኋላ ወዲያውኑ ወደ ተፈጥሯዊ ልጅ የማፍራት ችሎታዋ ትመለሳለች፡፡ ስታይል ሴቶች መካን እንዲሆኑ አያደርግም፡፡

አይፕላን  ጡት በሚጠቡ ህፃናት ላይ ተቅማጥ አያመጣም፡፡