ዲኬቲ ኢትዮጵያ በቤተሰብ እቅድ ላይ የሚሰሩ ጋዜጠኞችን አወዳድሮ ሸለመ
ዲኬቲ ኢትዮጵያ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ዘዴዎችን በስፋት ለማስተዋወቅ በሚያደርገው ጥረት ሀገር አቀፍ የጋዜጠኞች ሽልማት ፕሮግራም በታህሳስ ወር 2013 ዓ.ም አካሂዷል፡፡ በሀገሪቱ ግንባር ቀደም ለሆነው የማህበራዊ ግብይት ድርጅት በአይነቱ የመጀመሪያ በሆነው ውድድር ከመላው ሀገሪቱ የተውጣጡ 17 ጋዜጠኞች ስራዎቻቸውን አቅርበዋል፡፡
ከዘርፉ ምሁራን፣ የጤና እና የመገናኛ ብዙኋን ባለሙያዎች የተውጣጣ ቡድን የቀረቡትን ስራዎች በጥንቃቄ ከገመገመ በኋላ አምስት አሸናፊዎችን ለይቷል፡፡ አሸናፊዎቹም የገንዘብ፣ የሞባይል ስልክ እና መቅረፀ ድምፅ ሽልማቶች የተበረከተላቸው ሲሆን ሙሉ ወጪያቸው ተሸፍኖም የሁለት ቀን የጤና አዘጋገብ ስልጠና ወስደዋል፡፡
የዲኬቲ ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ማይክል ኢቫንስ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ዘዴዎችን ለህብረተሰቡ በማስተዋወቅ ረገድ የጋዜጠኞች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
“ፕሬሱ እና ጋዜጠኞች ለህዝቡ፣ ለአንባቢዎቻችሁ እና ለተመልካቾቻችሁ ከመንግስት እና ከሌሎች ተመሳሳይ ድርጅቶች ጋር በመሆን ሰዎች የተሻለ ሕይወት እንዲኖሩ ዕድል በመስጠት ሕይወታቸውን እንዲያቅዱ የሚያስችል የጤና እና የቤተሰብ እቅድ ዘዴ የትምህርት መርሃግብርን ለማስፋፋት እየሰራን መሆኑን እንድታሳውቁልን እንፈልጋለን ፡፡” ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ፡፡
የዲኬቲ ኢትዮጵያ የማርኬቲንግ ክፍል ኃላፊ ወ/ሮ እመቤት አቡ በበኩላቸው የሽልማት ፕሮግራሙ በጋዜጠኞችና ተደራሾቻቸው ዘንድ በቤተሰብ እቅድ ላይ ያተኮሩ ውይይቶችን በማስፋት ትክክለኛ የሆነ የመረጃ ፍሰት እንዲኖር ማስቻልን ያለመ ነው ብለዋል፡፡
“የምንፈልገውን አይነት የባህርይ ለውጥ ለማምጣት ቀጣይነት ያለው የመረጃ ፍሰት ያስፈልጋል፡፡ የእናንተን አጋርነት የምንፈልገው አዚህ ጋር ነው” ያሉት ወ/ሮ እመቤት ዲኬቲም ለጋዜጠኞች አስፈላጊውን መረጃ ለማቅረብ ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በቤተሰብ እቅድ ላይ የምታቀርቧቸው ተከታታይ ዘገባዎች የእናቶችና ህፃናትን ሞት ከመቀነስ ባሻገር ጤነኛና ደስተኛ ቤተሰብ እንዲኖር ያስችላልም ነው ያሉት፡፡
በሽልማት መርሃ ግብሩ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት በጤና ሚኒስቴር የእናቶችና ህፃናት ጤና እና የስነምግብ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶክተር መሰረት ዘላለም ኢትዮጵያ በተለይ ባለፉት ሁለት አስርት አመታት በቤተሰብ እቅድ ረገድ እመርታ ማሳየቷን ተናግረዋል፡፡
የዘመናዊ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ተጠቃሚዎች 41 በመቶ መድረሳቸውን የተናገሩት ዳይሬክተሯ አሁንም ብዙ ስራ እንደሚቀር አክለዋል፡፡
ያልተሟላ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ፍላጎት 22 በመቶ ነው ያሉ ጋዜጠኞች ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ሆነው ይሄን ችግር ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት መቀጠል እንዳለባው አሳስበዋል፡፡ በተለይም ተደራሽነትን ከማስፋት አኳያ ሚዲያው ትልቅ ስራ እንዳለበት በመጠቆም፡፡
ከአሸናፊዎቹ መካከል አንዱ የሆነው ጋዜጠኛ ወንድማገኝ በቀለ ሽልማቱ ጋዜጠኞች በጉዳዩ ላይ ይበልጥ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ እንደሚያነሳሳቸው ተናግሯል፡፡