Skip links
በአፍ የሚወሰዱ እንክብሎች

ቾይስ

ቾይስ በአፍ የሚወሰድ ባለጥምር አካላዊ ቅመም የእርግዝና መከላከያ እንክብል ሲሆን፤ የተሰራውም በተፈጥሮ በሴቶች አካል ውስጥ የሚመረቱትን ኤስትሮጅን እና ፕሮጀስትሮን አካላዊ ቅሞች (ሆርሞኖች) ከሚመሳሰሉ በጣም ዝቅተኛ መጠን ካላቸው ኤስትሮጅን እና ፕሮጀስቲን የተባሉ በሳይንሳዊ መንገድ የተፈበረኩ ንጥረ ነገሮች ነው፡፡

በቾይስ እሽግ ውስጥ የሚገኙት የእርግዝና መከላከያ እንክብሎች ሁሉም ባለእኩል መጠን የኤስትሮጅን እና ፕሮጀስቲን ይዘት አላቸው፡እያንዳንዱ የቾይስ እሽግ ባለ 28 ፍሬ ሲሆን፤ ይዘታቸው ሌቮኖርጀስትሪል 0.15 ሚ.ግ + ኢትናይልእስትራዲዮል 0.03 ሚ.ግ የሆነ 21 ነጭ የእርግዝና መከላከያ እንክብሎች እና ይዘታቸው ፌረስ ፉማሬት 75 ሚ.ግ የሆነ 7 ቡኒ የአይረን እንክሎችን ይይዛል፡፡

አስተማማኝነቱ ምን ያህል ነው?

አስተማማኝነቱ እንደ ተጠቃሚዎቹ የአጠቃቀም ሁኔታ ይወሰናል፡: ሴቷ የቾይስ እንክብል የያዘውን አዲስ እሽግ ሶስት ቀናት እና ከዚያ በላይ ዘግይታ ከጀመረች ወይንም የእንክብል እሽጉን በምትጀምርበት ወይም በምትጨርስበት ቀናት አካባቢ ለሶስት ቀናት እና ከዚያም በላይ የእርግዝና መከላከያ እንክብሉን ሳትወስድ ከቀረች እርግዝና የመከሰት እድሉ ከፍተኛ ነው፡፡

የቾይስ እንክብል በትክክል ከተወሰደ እና አወሳሰዱ ላይ ችግር ከሌለ እንክብሉን ከሚጠቀሙ 1000 ሴቶች ውስጥ በመጀመሪያው ዓመት ውስጥ እርግዝና ሊከሰት የሚችለው በ 3ቱ ሴቶች ላይ ብቻ ነው፡፡ ይህም ከአንድ ከመቶ በታች ነው፡፡

የቾይስ እንክብል ስትጠቀም የነበረች ሴት እንክብሉን መውሰዷን በመተው ለማርገዝ ብትፈልግ ወዲያውኑ ማርገዝ ትችላለች፡፡

ቾይስ ኤች.አይ.ቪ ፣ ሄፓታይተስ ቢ እና ሲ የተሰኙ የጉበት በሽታዎችን ጨምሮ ከማናቸውም ተላላፊ የአባላዘር በሽታዎች አይከላከልም፡፡

ጤና ነክ ጥቅሞች

ቾይስ እርግዝናን ከመከላከል በተጨማሪ የሚከተሉትን የጤና ችግሮች ለመከላከል ይረዳል፡-

  • የማህፀን ግድግዳ ካንሰር
  •  የእንቁልጢ ካንሰር
  •  የማህፀን ቁስለት
  •  ከወር አበባ መዛባት እና መብዛት ጋር የተያያዙ የደም ማነስ ችግሮችን
  • የሚከተሉትን ደግሞ ይቀንሳል፡-
  • በወር አበባ ጊዜ የሚከሰተውን የሆድ ቁርጠት
  • በውጻት ጊዜ የሚፈጠር የህመም ስሜት
  • በሰዉነት ወይም በፊት ላይ የጸጉር መብዛትን ይቀንሳል

ቾይስን መጠቀም የሚችሉት እነማን ናቸው

ቾይስ በአጠቃላይ ለሁሉም ሴቶች ተስማሚ እና ምቹ የእርግዝና መከላከያ ዘዴ ነው፡፡ ቾይስን መጠቀም የሚችሉ ሴቶች፡-

  • ልጅ ያላቸው ወይም የሌላቸው
  • ያገቡ ወይም ያላገቡ
  • አፍላ ወጣቶች እና ከ 40 ዓመት በላይ የሆናቸው ሴቶችን ጨምሮ በማንኛውም የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሴቶች
  • ፅንስ ያቋረጠች ወይም ያስወረዳት ሴት
  • የደም ማነስ ያለባቸው ወይም በፊት የነበረባቸው ሴቶች
  • የፀረ ኤች.አይ.ቪ መድሀኒት ቢወስዱም ባይወስዱም ኤች.አይ.ቪ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ ያለባቸው ሴቶች ቾይስንበአስተማማኝነት መጠቀም ይችላሉ፡፡
  • ሴቶች ቾይስን ፡

ምንም የማህፀን በር እና  የማህፀን አካባቢ እንዲሁም ምንም ዓይነት የላቦራቶሪ ምርመራ ሳያደርጉ ለእርግዝናመከላከያነት መጠቀም መጀመር ይችላሉ፡፡

ቾይስን መጠቀም የማይችሉት እነማን ናቸው

  • ያረገዘች ወይም እንዳረገዘች የምትጠረጠር ሴት
  • ባለፈው 3 ወራት ጊዜ ውስጥ የወለደች እናት
  • ከወለደች 6 ወራት ወይም ከዚያ በታች የሆናት የም ታጠባ እናት
  • በሳንባ ውስጥ የደም መርጋት ካለ ወይም ከነበረ
  • ከዚህ በፊት በጭንቅላት እና የደም ስሮች ላይ የደረሰ አደጋ ከነበረ
  • የልብ እና የልብ ቧንቧ ህመም ካለ ወይም ከነበረ
  • ከፍተኛ የሆነ የደም ግፊት ያለባቸው ሴቶች
  • ከደም ዑደት ጋር የተቆራኘ የስኳር በሽታ ካለ
  • ከነርቭ ጋር የተያያዘ የራስ ም ታት ካለ
  • የጡት ካንሰር ካለ
  • የጉበት ካንሰር ካለ
  • የጉበት ህመም ችግር ካለ
  • በቀን ከ15 ሲጋራዎች በላይ የሚያጨሱ እና ዕድሜያቸው ከ35 ዓመት በላይ የሆነ ሴቶች
  • እንክብሉ የተሰራበት ንጥረነገሮች እንደማይስማማት የተረጋገጠ ሴት

የጎንዮሽ ችግሮች

አንዳንድ ተጠቃዎች እነዚህን ሪፖርት አድርገዋል

  • መጠነኛ የራስ ምታት
  • ድብርት
  • ማቅለሽለሽ (በአብዛኛው ከ2-3 ወራት ለሚሆን ጊዜ ከተጠቀሙ በኋላ ይህ ስሜት ይጠፋል)
  • የጡት መደደር
  • የክብደት መጨመር ወይም መቀነስ
  • የስሜት መለዋወጥ (በጣም አልፎ አልፎ)
  • ብጉር (ሊሻሻል ወይም ሊባባስ የሚችል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ግን ሊሻሻል የሚችል)

ስለ ቾይስ ተደጋግመው የሚጠየቁ ጥያቄዎች

ሴቷ በዚያ ቀን የግብረ ስጋ ግንኙነት ብታደርግም ባታደርግም እንክብሉን በየቀኑ መውሰድ አለባት፡፡

አንድ ሴት ቾይስ መጠቀም ካቆመች በኋላ ወዲያውኑ ወደ ተፈጥሯዊ ልጅ የማፍራት ችሎታዋ ትመለሳለች፡፡ ቾይስ ሴቶች መካን እንዲሆኑ አያደርግም፡፡

ቾይስ በእርግዝና ላይ ምንም የሚያስከትለው ችግር የለም፡፡ ሴቶች አካለ ጎዶሎ ወይም መንታ ልጅ እንዲወልዱም ምክንያት አይሆንም፡፡

ቾይስ በሴቶች የግብረ ስጋ ግንኙነት ፍላጎት ላይ ምንም ዓይነት ለውጥ አያስከትልም፡፡

እያንዳንዱ የቾይስ እንክብል በየቀኑ ስለሚሟሟ በጨጓራ ወይም በሰውነት ውስጥ አይከማችም፡፡