Skip links

ኮቪድ-19 ያልበገረው የዲኬቲ ኢትዮጵያ የምርቶች አቅርቦት

ኮቪድ-19  በመጋቢት ወር 2012 ዓ.ም አለም አቀፍ ወረርሽኝ መሆኑ ሲታወጅ ፈንዶችና ትኩረቶች ወደ ቫይረሱ ስለሚዞሩ የቤተሰብ ዕቅድ እና የስነተዋልዶ ጤና ፕሮግራሞች በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚቀንሱ ብሎም በሴቶች ጤና ላይ በበርካታ አስርት አመታት ጥረት የተመዘገቡ ለውጦች ሊዳከሙ እንደሚችሉ ብዙዎች ስጋታቸውን ገልፀው ነበር፡፡

ከ18 ወራት ቆይታ በኋላ አንዳንዶቹ ስጋቶች እውን ሆኑ፡፡ ሰፊ የሆነ የትራንስፖርት መስተጓጎል እና የሰራተኞች ቅነሳ፣ በደረቅ ጭነቶች እንቅስቃሴ ላይ የታዩ ፈጣን ለውጦች፣ በቻይና እና በህንድ የታዩ የፖሊሲ ለውጦችና ገደቦች እንዲሁም የዋጋ ንረት በአቅርቦትና ፍጆታ ላይ ተፅእኖ አሳድረዋል[1]፡፡

እንደ የተባበሩት መንግስታት የስነህዝብ ፈንድ (ዩኤንኤፍፒኤ) ሪፖርት ከሆነ “መረጃዎች ቫይረሱ በቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ላይ የደረሰው ጫና አነስተኛና ከሚያዚያ እስከ ግንቦት 2012 ዓ.ም ባለው አጭር ጊዜ  ብቻ የቆየ መሆኑን ያሳያሉ”፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሁኔታም ይሄንኑ ነው የሚያሳየው፡፡ የቤተሰብ ዕቅድ እና የስነተዋልዶ ጤና አገልግሎት አቅርቦትና ፍጆታው በመጀመሪዎቹ ወራት ከገጠመው መስተጓጎል በኋላ መረጋጋት ታይቶበታል፡፡ በሀገሪቱ ከመንግስት ቀጥሎ ለግሉ ዘርፍ ከፍተኛው የቤተሰብ እቅድና የስነተዋልዶ ጤና ምርቶች አቅራቢ በሆነው ዲኬቲ ኢትዮጵያ የስራ አንቅስቃሴ ውስጥም የታየው ተመሳሳይ ነው፡፡

“በዋንኛነት ወረርሽኙ ያስከተለው ሁለት ነገሮችን ነው፡፡” ይላሉ አቶ ንጉሴ ገብረፃዲቅ የዲኬቲ ኢትዮጵያ ብሄራዊ ኦፐሬሽኖች ዳይሬክተር፡፡

“የመጀመሪያው ሴቶች በክሊኒክ ውስጥ ከሚሰጡ እንደ በክንድ ቆዳ ስር የሚቀመጡ የወሊድ መከላከያ አይነት አማራጮች ይልቅ ፊታቸውን ወደ በአፍ የሚወሰዱ የወሊድ መከላከያዎች ማዞራቸው ነው፡፡”

“ሁለተኛው ዋነኛ ምርት አቅራቢዎች በሰራተኛ እጥረት ፣ በጥሬ ዕቃ አቅርቦት መዘግየት እና በዋጋ ንረት ምክንያት ተፅእኖ አድሮባቸዋል፡፡”

“ይሄ ተፅእኖ በተለይ በመርፌ በሚሰጥ የወሊድ መከላከያ ላይ ታይቷል፡፡”

ዲኬቲ ኢትዮጵያ በመርፌ የሚሰጥ የወሊድ መከላከያ የሚያስገባው ባንኮክ ታይላንድ ካለው ኤ.ኤን.ቢ ላብራቶሪስ ኩባኒያ ነው፡፡ በእነዚህ የቤተሰብ እቅድ ዘዴዎች ላይ ከሚያዚያ 2011 ጀምሮ የነበረው የአቅርቦት ችግር በወረርሽኑ በመባባሱ ምክንያት ኢትዮጵያን ጨምሮ በአለም ዙሪያ እጥረትን አስከትሏል፡፡

አጋር ክሊኒኮች

ወደ ዲኬቲ አጋር ክሊኒኮች የሚመጡ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ቁጥር በድርጅቱ ጠቅላላ የምርት ስርጭት ላይ የታዩ አንዳንድ ለውጦችን ያሳያል፡፡ ወደ ክሊኒኮቹ የሚመጡ የአዲስ ተጠቃሚዎች አመታዊ ቁጥር እ.ኤ.አ በ2020 የ13 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል፡፡ የአጠቃላይ ተጠቃሚዎች ቁጥር ደግሞ በ3በመቶ ቀንሷል፡፡

በመላው ኢትዮጵያ ከ100 በላይ ክሊኒኮችን ያቀፈው የአጋር ክሊኖኮች ኔትወርክ አስተባባሪ እና የብሄራዊ ኪይ አካውንትስ ማኔጀር አቶ ዳኛቸው አለማየሁም የሚያረጋግጡት ይህንኑ ነው፡፡

“ወረርሽኑ በጀመረባቸው የመጀመሪያ ወራት ሴቶችና ጥንዶች ከክሊኒኮች ርቀው ነበር፡፡ ከ6-8 ወራት ቆይታ በኋላ ግን በተደረጉ የህብረተሰብ ጤና ማሻሻያ ተግባራት የተጠቃሚዎችን ቁጥር ወደነበረበት መመለስ ተችሏል፡፡”

ጠቅላላ የምርት አቅርቦት መጠኑም መረጋጋት እና በአንዳንድ ምርቶች ላይም ጭማሪ አሳይቷል፡፡ በአፍ የሚወሰዱና ድንገተኛ የእርግዝና መከላከያዎች እንደየቅደም ተከተላቸው እ.ኤ.አ በ2019 ከነበረው አንፃር የ17 እና የ64 በመቶ እድገት አሳይተዋል፡፡

REFERENCES

[1] Reproductive Supplies Coalition. “Building Resilient Sexual and Reproductive Health Supply Chains During Covid-19 and Beyond”. April 2021. https://www.jsi.com/resource/building-resilient-sexual-and-reproductive-health-supply-chains-during-covid-19-and-beyond-community-roadmap-for-action-and-technical-findings/

[2] UNFPA. “Impact of COVID-19 on Family Planning: What we know one year into the pandemic” [Technical Note],
March 2021. https://www.unfpa.org/resources/impact-covid-19-family-planning-what-we-know-one-year-pandemic