Skip links

ዳግም ያቆጠቆጠ ህልም እና የሴትኛ አዳሪዋ ህይወት

በርካታ አሳዛኝ አጋጣሚዎች ናቸው ሰላም አበበን (ስሟ የተቀየረ) ወደ ወሲብ ንግድ ስራ የከተቷት፡፡

በስድስት አመቷ እናቷ ሞቱ፡፡ አባቷ ለዘመድ ጥሏት ሚስት አግብቶ አዲስ ህይወት መሰረተ፡፡ በፈተናዎች ውስጥም ሆና ሰላም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን አጠናቃ በዩኒቨርስቲ መግቢያ ፈተና ጥሩ ውጤት አመጣች፡፡

ትምህርቷን ከመቀጠል ይልቅ ግን በ18 አመቷ ተዳረች፡፡ ባለቤቷ ጠጪ እና ቀናተኛ በመሆኑ ትዳራቸው ረጂም ግዜ አልዘለቀም፡፡ አንድ ልጅ ወልደው ተፋቱ፡፡

የ24 አመቷ ሰላም ኑሮን ለመግፋት ስራ ስትፈልግ  በአንድ ሆቴል ውስጥ አስተናጋጅነት አገኘች፡፡

“ያለምንም ስልጠና ልሰራው የምችለው ስራ ያገኘሁት አስተናጋጅነትን ነው፡፡ነገር ግን ክፍያው ዝቅተኛ በመሆኑ የተነሳ አስተናጋጅነት ከባድና መሰረታዊ ወጪዎቼን እንኳን ለመሸፈን በቂ አልነበረም፡፡” የምትለው ሰላም በዚህ ምክንያት ለሴተኛ አዳሪነት መዳረጓን ትናገራለች፡፡

ደንበኖቿን በሆቴሎች ውስጥ የምታገኘው ሰላም አንዳንድ ጊዜም በስልክ ጥሪም ታስተናግዳለች፡፡ ኮቪድ ከመምጣቱ በፊት በቀን አንድ ወይ ሁለት ደንበኞች አታጣም ነበር፡፡ “ከኮቪድ በኋላ ግን ስራው ቀዘቀዘ፡፡”

በዚህ ስራ ውስጥ ብዙ ፍርሃቶች አሉባት፡፡ ዋናው ፍርሃቷ ግን ኮንዶም መጠቀም በማይፈልጉ ወንዶች ምክንያት በኤች አይ ቪ እንዳትያዝ ነው፡፡ በዚህም በየሶስት ወሩ ምርመራ ታደርጋለች፡፡ ለአሁኑ ውጤቷ ኔጌቲቭ ቢሆንም ፍርሃቷ ግን እንዳለ ነው፡፡ ድበደባ እና ህይወትን ማጣትም ያሰጋታል፡፡

በዚህ አስቸጋሪ ህይወት ውስጥ እያለች ያገኘችው አንድ ጥሩ አጋጣሚ የዲኬቲ ኢትዮጵያ ዋይዝ አፕ ፕሮግራምን ነው፡፡ የፕሮጀክቱ ማቆያ ማእከላት ቀን ቀን ለማረፊያ የሚሆኑ ክፍሎች ሲያስፈልጓት፣ የጤና አገልግሎት ስትሻ፣ መዝናናት እና ልብሶቿን ማጠብ ስትፈልግ ጥሩ መዳረሻ ሆነዋታል፡፡ ለዚህም ነው ሰላም “ዋይዝ አፕ ለእኔ ቤቴ ነው” የምትለው፡፡

“ዋይዝ አፕ የቀን ወጪዎቼን በመቀነስ ገንዘብ እንድቆጥብ አግዞኛል፡፡ ከኮቪድ በፊት በቀን ከ500-600 ብር እሰራ ነበር፡፡ ያም ሆኖ ግን ለመቆጠብ አስቸጋሪ ነበር፡፡ ይህን ፕሮጄከት ከጀመርኩ ወዲህ ነው መቆጠብ የጀመርኩት፡፡”

አሁን ሰላም ማታ ማታ እየሰራች ቀን ቀን አካውንቲንግና ፋይናንስ መማር አቅዳለች፡፡ ለአንድ ኮሌጅ አመልክታ የመግቢያ ፈተና ለመውሰድ እየተጠባበቀች ነው፡፡ ዲግሪዋን ካገኘች በኋላ በተመረቀችበት ሙያ ለመስራት ወይም የራሷን ቢዝነስ ለመክፈት ሀሳብ አላት፡፡

ጥሩ ባል ካገኘሁ አሁንም ለማግባት እፈልጋለሁ የምትለው ሰላም ነገር ግን የቀደሞ ትዳሯን ከመድገም ይልቅ ልጇን ብቻዋን ማሳደግ እንደምትመርጥ ነው የገለፀችው፡፡

ዋይዝ አፕ ሴትኛ አዳሪዎች ኮንዶምን በመጠቀም ራሳቸውን ከኤችአይቪ እንዲከላከሉ ፣ በቫይረሱ የተጠቁት ደግሞ ህክምና እና አንክብካቤ እንዲያገኙ ማስቻል ላይ ያተኮረ ፕሮጀክት ነው፡፡