Skip links

ዲኬቲ “ግልፅ የህይወት እቅድ ኖሮኝ በጤና እንድመረቅ አግዞኛል”፤ ወጣት አማኑዔል

ለመጀመሪያ ጊዜ የዲኬቲ ኢትዮጵያን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፕሮጀክት ስልጠና የታደመው ለጫት የሚሆን አበል ለማግኘት ነበር፡፡ ነገር ግን ስልጠናው ህይወቱን ለመለወጥ ትልቅ አጋጣሚ ሆነለት፡፡ “ፕሮጀክቱ ግልፅ የህይወት እቅድ ኖሮኝ በጤና እንድመረቅ አግዞኛል ይላል” የትናንቱ ተማሪ የዛሬው የማህበራዊ ሚዲያ ባለሙያ አማኑዔል አክሊሉ፡፡

የ28 አመቱ ወጣት ባህርዳር ነው ተወልዶ ያደገው፡፡ በጥሩ ውጤት ተመርቆ አርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ ከገባ በኋላ ግን በትምህርቱ መሰላቸት በመጀመሩ ውጤቱ ማሽቆልቆሉን ተያያዘው፡፡ አብዛኛውን ግዜ ትምህርቱ ላይ ሳይሆን ከጓደኞቹ ጋር ከተማ ወጥቶ ማሳለፍ ላይ አዘወተረ፡፡

“በግዜው በጣም በሱስ ተጠምጄ ነበር፡፡ ብዙ አጨሳለሁ እጠጣለሁም፡፡ ብዙ ለአደጋ አጋላጭ ባህርያት ውስጥ ገባሁ፡፡ በህይወቴ ምንም ግብ አልነበረኝም፡፡”

አማኑዔል በ2006 ዓ.ም በዩኒቨርስቲው ውስጥ በዲኬቲ ኢትዮጵያ የተዘጋጀ ፕሮግራም ቀልቡን ሳበው፡፡ ፕሮግራሙ ለዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ደረጃውን የጠበቀ መረጃ በመስጠት ሀላፊነት የጎደላቸው ወሲባዊ ባህርያት፣ ያልተፈለገ እርግዝናን እና በግብረስጋ ግንኙነት የሚተላለፉ የአባላዘር በሽታዎችን ለመቀነስ ያለመ ነበር፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፕሮጀክቱ ለአማኑዔል የህይወት ክህሎት አለመኖር፣ እቅድ አልባ መሆንና ሱሰኝነት ወደ አደገኛ ባህርያት እንደሚወስዱ ግልፅ አድርጎለታል፡፡

“ዲኬቲዎች ማስተላለፍ የሚፈልጉትን መልዕክት በኪነጥበብ እና ታሪክ ነገራ አዋዝተው የሚያቀርቡበት   ግሩም ዘዴ አላቸው፡፡ ለነፍሴ ቅርብ የሆነ ነገር ነበር የሚነግሩኝ፡፡ ምንም እንኳ መጀመሪያ ላይ አላማዬ ሌላ ቢሆንም አቀራረቡ ስለተመቸኝ ይበልጥ እየተሳብኩ እና እየገባሁበት መጣሁ፡፡ የሆነ ነገር መስጠት እንዳለብኝም ወሰንኩ፡፡ በመስጠት ውስጥ ደግሞ ብዙ ነገርን አገኛለሁ፡፡”

“ስለዚህ ፕሮጀክት ልለው የምችለው አንድ ትልቅ ነገር ለወጣቶች እድል ይሰጣል፡፡ እኛን እንደ ተጎጂዎች አልነበረም የሚያየን፡፡ እንደዚያ ቢሆን ትቶ ለመሄድ የመጀመሪያው የምሆነው እኔ ነበርኩ፡፡ችግሩ ብቻ ሳይሆን መፍትሄውም እኔ ጋር እንዳለ አሳይቶኛል፡፡”

በአጭር  ጊዜ አማኑኤል በፕሮጀክቱ ውስጥ ከሚሳፉ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ግንባር ቀደሙ ሆነ፡፡ በዲኬቲ ማህበራዊ ድረገፅ ተማሪኔት ላይም ንቁ ተሳታፊ ሆነ፡፡

“የዩኚቨርስቲ ተማሪዎች ስለ ስነተዋልዶ ጤና ብዙ ነገር ቢያውቁም በየጊዜው የማንቂያ ስራ ሊሰራባቸው እንደሚገባ ተገነዘብን፡፡ ኮንዶም መጠቀም እንዳለብን ብናውቅም እንዘነጋዋለን፡፡ በዚህ ላይ የሚሰራው የማንቂያ ስራ ዝም ብሎ ኮንዶም ተጠቀሙ፣ በፍቅር አጋሮቻችሁ ላይ አትወስልቱ፣ አንድ ለአንድ ተወሰኑ የሚል ብቻ መሆን የለበትም፡፡ ሰዎች እራሳቸውን መጠበቅ እንዳለባቸው የሚያስታውሱ ጨዋታዎችን እና ልዩ ልዩ መንገዶች እንፈጥራለን፡፡”

አማኑዔል በ2009 ዓ.ም በኤሌክትሪካል እና ኮምፒውተር ምህንድስና ተመረቀ፡፡ አሁን በግሉ በማህበራዊ ሚዲያ ባለሙያነት ይሰራል፡፡

በ2012 ዓ.ም ትዳር የመሰረተው አማኑዔል ከባለቤቱ ጋር በሁለት አመት ውስጥ የመጀመሪያ ልጃቸውን ለመውለድ አቅደዋል፡፡ ሁሉም ነገር በእቅዱ መሰረት እየሄደ ነው፡፡

የዲኬቲ ኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የስነተዋልዶ ጤና ፕሮጀክት እ.ኤ.አ ከ2009 ጀምሮ ከ28 ዩኒቨርስቲዎችና የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆች ጋር በትብብር ሲተገበር የቆየ ሲሆን በዚህም እስከ 2020 ድረስ ብቻ ከ1.2 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን መድረስ ችሏል፡፡ ከ2.9 ሚሊዮን በላይ ኮንዶሞች እና 54000 በአፍ የሚወሰዱ ወርሃዊ የእርግዝና መከላከያ እንክብሎችም ተሰራጭተዋል፡፡